top of page
Website design 1.jpg
Search

የሲቪል ዜጎችን መረጃ የማግኘት እና የመገናኘት መብት በማፈን፤ ንጹሃንን በመጨፍጨፍ የሚቆም የአማራ ሕዝብ የኀልውና ትግል የለም!(ከ አንድነት ለአማራ ኀልውና [አንድነት] የተሰጠ አስቸኳይ መግለጫ)


የጦር ወንጀለኛው የብልጽግናው አገዛዝ በአማራ ሕዝብ ላይ የከፈተው ይፋዊ ጦርነት 3ኛ ዓመቱን ባስቆጠረበት በዚህ ጊዜ፣ በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት በማቋረጥ፣ የሲቪል ዜጎችን መረጃ የማግኘት እና የመገናኘት መብት አፍኗል፤ በንጹሃን ላይም የጅምላ ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በተለይም ከጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ያለፉት ሰባት ቀናት በሸዋ ቀጠናዎች፣ ምዕራባዊ የወሎ ቤተ አማራ ክፍል፣ በምስራቅ ጎጃምና በምዕራብ ጎንደር የገጠርና መለስተኛ የወረዳ ከተሞች ድረስ ሙሉ በሙሉና በከፊል የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ፣ በአካባቢዎቹ የቀጠለው የንጹሃን ጭፍጨፋ መረጃው የታፈነ በመሆኑ፣ እልቂቱን የተባባሰ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ጥር 28 ቀን 2018 ዓ.ም በወሎ ቤተ አማራ ወግዲ ወረዳ፤ ጥር 29 ቀን 2018 በሸዋ መርሃ ቤቴ አውራጃ ደራ ወረዳ እንዲሁም በይፋትና ጥሙጋ አውራጃ በኤፍራታና ግድም በብልጽግናው አገዛዝ በተፈጸሙ ጭፍጨፈቻዎች አንድ መቶ የሚደፈርሱ ንጹሃን ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል፡፡ ይህ መረጃ ከፊል ስልክ በሚሰራባቸው አካባቢዎች ብቻ የተገኘ ሲሆን፤ አረመኔው አገዛዝ የሲቪል ዜጎችን መረጃ የማግኘትና የመገናኘት መብት በማፈን እየፈጸማቸው ያሉ የጦር ወንጀሎች ከዚህም በላይ የከፋ እንደሚሆን ይታወቃል፡፡

የጦር ወንጀለኛው የብልጽግናው አገዛዝ ከቀደምት ባህሪዎቹ ስንነሳ ከፋኖ ከፍተኛ ምት ሲደርስበት ንጹሃንን ማጥቃት፤ የማኀበራዊ ተቋማትን ማውደም፤ የአርሶ አደሮችን ማሳ ማቃጠል፤ የእምነት ቦታዎች ላይ ጥቃት መፈጸም የተለመደ የጦር ወንጀል ድርጊቶቹ ናቸው፡፡

የዕለት ኑሯቸውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በሚሉ፣ ከውጊያው አውድ ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ሰላማዊ ወገኖቻችንን በጅምላ ገድሏል፣ ንብረታቸውን አውድሟል፡፡ መሰረተ ልማቶችንም አፈራርሷል፡፡

በተለይም በታሪካዊውና የአባቶቻችን ርስት በሆነው የሸዋ ምድር የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት በአመዛኙ ክፍል የተቋረጠ በመሆኑ በጦር አውድማ ያልተሳተፉ ንፁሀን በጅምላ በድሮን፣ በመድፍና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች እየተፈጁ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ በውስጥም ሆነ በውጭ ያለው የአማራ ኃይል፣ የአማራ ሕዝብ ወዳጆችና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ዝምታ መምረጣቸው አሳሳቢ ሆኗል፡፡

ሴቶች፣ ህጻናት፣ እናቶች፣ አባቶች፣ አዛውንቶች፣ ያልታጠቁ ንጹሃን በአማራዊ ማንነታቸው ብቻ የጥቃት ተጋላጭ ሆነው በሰማይ በድሮን፣ በምድር በዘመናዊ ተወንጫፊ ከባድ መሣሪያዎች በጅምላ ሲጨፈጨፉ በዝምታ ማየት ሊቆም ይገባል!!

ከሁሉም በላይ አሳሳቢ ነገር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አገዛዙ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጽማቸውን ማንነት ተኮር ወንጀሎች ትኩረት እንደነፈጋቸው መሆኑ ነው።

ከመቼውም የበለጠ ወራሪ ኃይሉ የጦር ወንጀሉ እንዳይጋለጥ መረጃዎችንና የግንኙነት ዘዴዎችን አፍኖ፣ የጦር ወንጀል እየፈጸመ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ የወገን ዝምታ፤ ዓለማቀፉ ማኀበረሰብ የአማራን ስቃይ እንዲዘነጋው አድርጎታል፡፡

ዛሬም እንደትናንትናው የአማራ ሕዝብ ስቃይና መከራ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትኩረት የተነፈገው በወገን ዝምታ፣ አቅምና ችሎታችንን ወደአንድ ቋት በማምጣት መሬት ላይ የቀጠለውን በደል በተደራጀ መልኩ ባለማስረዳታችን ነው፡፡

ስለሆነም፡-

የአገዛዙን የጦር ወንጀል ለማጋለጥ ሁሉም አማራና የአማራ ትግል ደጋፊዎች ለዓለማቀፉ ማኀበረሰብ በተደራጀ ሁኔታ ድምጻችንን እንድናሰማ፤ በተለይም የአማራ ማኀበራትና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች በበርካታ የአማራ አካባቢዎች የሰልክ ግንኙነትና ኢንተርኔት ተቋርጦ በአገዛዙ የሚፈጸመውን የጦር ወንጀል ለዓለማቀፉ ማኀበረሰብ በተደራጀ መልኩ የማጋለጥ ኃላፊነታችንን በጋራ አቅም እንድንወጣ አንድነት ጥሪውን ያቀርባል፡፡


የብልጽግናው አገዛዝ የሲቪል ዜጎችን መረጃ የማግኘት እና የመገናኘት መብት በማፈን፤በንጹሃን የአማራ ተወላጆች ላይ እየፈጸማቸው ያሉ የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ ሌሎች የጦር ወንጀሎችንም የሚመረምር ገለልተኛ የሆነ ዓለምአቀፋዊ አጣሪ ቡድን እንዲቋቋም እና በውጤቱ መሠረት ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፡፡


በአጠቃለይ ዓለም-አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ ትግል፣ በተለይም ይዘቱ ልዩ የሆነውን የአማራ ሕዝብን የፀረ-ጄኖሳይድ ራስን የመከላከል የህልውና ትግል በአግባቡ እንዲረዳው እና ጥርት ያለ አቋም እንዲይዝ ጥሪ እናቀርባለን፡፡


በብልጽግናው አገዛዝ የሚመራው ሥርዓተ መንግሥት ክሽፈት በሀገራዊ ደረጃ ከመወሰን አልፎ ወደ ጂኦ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል እያደገ ይገኛል፡፡ የዚህ መነሻ ሥረ-ምክንያት በአጠቃላይ ብሄር ተኮር፣ በተለይ ደግሞ አማራ ጠል በሆነው ሥርዓታዊ ዘረኛ ፖሊሲ የሚመራ እንደሆነ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሰወረ ባለመሆኑ፣ በዚህ ልክ መፍትሄ እንዲመጣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት መናበብ አና ተቀናጅቶ መሥራት ግድ ይላል።

ስለዚህም፣ አማራ ላይ ያነጣጠረውን ብሄር ተኮር የገዢው ፓርቲ የጥላቻ ፖለቲካ ከስር መሠረቱ የሚነቅል የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ እና የአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላ የኢትዮጵያ ህዝብም ለ50 ዓመታት የናፈቁትን ሰላም እና ሥር-ነቀል ለውጥ እንዲጎናፀፍ፤ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲያመጣ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡


ድል ለአማራ ፋኖ!

ድል ለአማራ ሕዝብ!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

አንድነት ለአማራ ኅልውና (አንድነት)

የካቲት 2/2018 ዓ.ም.






 
 
 

Comments


bottom of page