በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ንቅናቄ (አፋብን) አመሠራረት ላይ የአንድነት ለአማራ ኅልውና (አንድነት) አቋም
- Amhara Unity
- Feb 8
- 4 min read

በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ንቅናቄ (አፋብን) አመሠራረት ላይ የአንድነት ለአማራ ኅልውና (አንድነት) አቋም
የአማራን ዘር ማጥፋት ድርጊት በሕወሃት እና በኦነግ ተፅፎ 3 አሥርተ ዓመታትን ከተሻገረዉ ሰነድ ተቀድቶ የሃገሪቱ ሕጋዊ መተዳደሪያ ከተደረገ “ሕገመንግሥታዊ ስርአት” ይመነጫል።
በዚህም እጅግ ብዙዎች በአማራ ማንነታቸዉ በጭካኔ ተጨፍጭፈዋል፣ በር ተዘግቶባቸው በቤቶቻቸዉ ውስጥ ተቃጥለዋል፣ ታርደዋል፣ ተወልደው ካደጉበት ቀዬ ተፈናቅለዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ታፍነዋል፣ በአስከፊ እሥር ቤቶች ታጉረዋል፣ ከፌዴራል የሥራ ቦታዎች በገፍ ተባረዋል።
“የግፍ ግፍ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” እንዲሉ ከሕወሃት ጋር የተደደረገውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ተከትሎ አገዛዙ የአማራን ክልል ወርሮ ሰላማዊውን የአማራ ሕዝብ በሰማይ በድሮን በምድር በእግረኛ ሠራዊቱ እየጨፈጨፈ፣ ሴቶችን እየደፈረ፣ ሠብሉን እያቃጠለበት ፣መንገዶችን እያፈረሰበት፣ ትምህርት ቤቶችንና የህክምና ጣቢያዎችን ለጦሩ ካምፕ በማድረግ ሕዝቡን ለረሃብና ለበሽታ ዳርጎት ይገኛል።
ከዚህ ፈርጀ ብዙ ጥቃት የእምነት ተቋማትም አላመለጡም። የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች እምነታቸውን እንደለመዱት በነፃነት እንዳይተገብሩ አገዛዙ ቤተ እምነቶችን እያቃጠለ፣ ንዋየ ቅድሳትን እየዘረፈ፣ ገዳማትን እያወደመ፣ አባቶች እና ምእመናን እየገደለ ይገኛል። በነባሩ የእስልምና እምነትም ላይም በተመሳሳይ ሁኔታ ጥቃት እያደረሰ ነው።በአጠቃላይ የአብይ አህመድ አገዛዝ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀልን በስፋት አጠንክሮ እየፈፀመ ይገኛል።
ይህንን ግዙፍ ጥቃት ለመከላከልና ጨርሶ ከመሰረቱ ለማስቆም ባለፉት 3 ዓመታት የአልሞት ባይ ተጋዳይ ትግል የጀመረው የአማራ ልጅ ፋኖ በየዕለቱ በየጦር አውዱ የሥርዓቱን ገዳይ ሠራዊት አይቀጡ ቅጣት እየቀጣ በድል ላይ ድል እየተቀዳጀ ይገኛል። ቢሆንም የፋኖን መስዋዕትነት እና በወገናችን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንዲሁም ትግሉን በአጭር ጊዜ ከግቡ ለማድረስ የፋኖ አንድነት መፈጠር እጅግ አስፈላጊ ነዉ። ስለሆነም የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) እና የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ሃይል (አፋብሃ) ከስመው የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ (አፋብን) የተሰኘውን መፍጠራቸዉ ይበል የሚያሰኝ እርምጃ ነዉ።
ድርጅታችን አንድነት ለአማራ ኅልውና (አንድነት) የፋኖን ተግባራዊ አንድነት በፅኑ ይደግፋል። ይህንንም ድርጅታችን ሲቋቋም ባወጣው መግለጫ ላይ እንደዋነኛ መርሁ አድርጎ በግልጽ አስቅምጦታል። ይሁን እንጂ አፋብን ከመመሥረቱ በፊትና ከተመሠረተ በኋላ ተድበስብሰዉ ሊታለፉ የማይችሉ በርካታ መመለስ ያለባቸው ሥጋት የሚያጭሩ አንገብጋቢ ጉዳዮዎች አሉ ብለን ስለምናምን ዋና ዋናዎቹን ከዚህ ቀጥለን መግለፅ እንወዳለን።
1ኛ. የአማራ ህልውና ለዘለቄታው ሊረጋገጥ የሚችለዉ በሥር ነቀል ወይም ሥርዓት ነቀል ለውጥ ብቻ ነው ብለን እናምናለን። ይህም ማለት አሁን ያለዉ ሕገመንግሥት ሲቀየርና እና በምትኩ ዘረኝነትን የሚጠየፍ፣ ሁሉንም ዜጋ በፍፁም እኩልነት የሚያስተናግድ፣ ሀገራዊ አንድነትን የሚያፀና፣ ፍትሀዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሕገመንግሥታዊ ስርአት ሲዋቀር እና በሥራ ላይ ሲውል ብቻ ነው ማለት ነው። ፋኖ ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ላይ ያለውም ይህንን ለማረጋገጥ ነው። አፋብን ግን ስለስር ነቀል ለዉጥ አቋሙ ግልጽ አይደለም። እንዳውም አንዳንድ የንቅናቄዉ “ውስጥ አዋቂ ደጋፊዎች” ሕገመንግስቱ “ለአማራ እጅግ ጠቃሚ ነው” ሲሉ በገሀድ እየሞገቱ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን አፋብን ከአማራ ታሪካዊ ጠላቶች ከሕወሃትና ኦነግ ጋር
አብሮ ለመሥራት ያለው አዝማሚያ የአደባባይ ምስጢር ነዉ! ከሌሎች በርካታ ማስረጃዎች በተጨማሪ በቅርቡ የንቅናቄው ም/ሊቀመንበርና የፖለቲካ ዘርፉ ሃላፊ ከማንኛውም የክልል መንግሥት ጋር እንሠራለን ብሏል። “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ ተገንጠይዋ ሕወሃትም የአማራ ርስት የሆኑትን ጠለምትን በከፊል፣ ራያን እስከቆቦ ሰሞኑን ወራለች። ወልቃይት ጠገዴን እንደገና ለመያዝ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው። የኦነግም አላማ መገንጠል ዋነኛ ግቡ ሲሆን አሁን ያለውን አፓርታይዳዊ ሥርዓት በመሰረታዊ መልኩ ሳይቀየር አብይ አህመድን እና ቡድኑን መቀየር ብቻ ነው።
በጥር 19/2018 የንቅናቄው የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ባወጣው መግለጫ ላይ “አንድ ወገን፣ አንድ ጠላት....በአብይ አህመድ አገዛዝ ላይ ብቻ ማነጣጠር...” የሚለው የሚያመላክተው ከላይ እንደጠቀስነው ከሕወሃትና ከኦነግ ጋር አፋብን ያለው ቁርኝት ነው። ይህ እጅግ በጣም አሳስቦናል።
2ኛ. በንቅናቄው ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን እንዲመሩ የተመደቡ አንዳንድ የቀድሞ የ”አፋብሃ” አመራሮች ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱባቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ባለፋት ሁለት አመታት የተናገሯቸውና ተመዝግበው የሚገኙ በሴራና በስብእና ገደላ የተካኑ ናቸው። እንዲሁም በፈጸሟቸውና ባስፈጸሟቸው ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች ምክንያትና ከነሱ የተለየ ሃሳብ ወይም አቋም በሚያስተናግዱ ፋኖዎች ላይ ዘመቻ በማስከፈትና ጉዳት በማድረስ የሚታወቁ ናቸው።
3ኛ. “ከክልሉ ውጭ” ስለሚኖረው የአማራ ህዝብ ህልውናን በተመለከተ ንቅናቄው በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም። ስለሆነም ንቅናቄው ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ አማሮች እስከአሁን ድረስ በተለያየ ፈርጅ ለአማራ የህልውና ትግል ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ዋጋ እየነፈገ ነው ማለት ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘና እንዲሁም ከላይ በተራ ቁጥር አንድ እንደተጠቀሰው ንቅናቄው ከሌሎች ክልሎች ጋር ለመነጋገርና ለመተባበር መወሰኑ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ሕገመንግሥት እውቅና እየሰጠ ነው ማለት ነው። ይህም ሌላ ሥጋታችን ነው።
4ኛ. በአፋሕድና በአፋብሃ የአንድነት ሂደት ላይ ከተሳተፉት ሽማግሌዎች ጀርባ ከአሁን ቀደም የአምባገነኑ አብይ አህመድን አገዛዝ በመደገፍ እንዲጠናከር ከፍተኛ ሚና በመጫወታቸው፣ “አማራ የሚባል ሕዝብ የለም!” ብለው የጻፉና አማራ ጠል ለሆኑ አገዛዞች በአምባሳደርነት እና በተለያዩ ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች በማገልገላቸው ከየአቅጣጫው ጥያቄ ሲነሳ እየተሰማ ነው። እኛም በበኩላችን ንቅናቄው ወደየት እያመራ ነው የሚል ሥጋት አለን።
5ኛ ቀደም ሲል የአፋብሃ ዛሬ የንቅናቄው ደጋፊዎች ሆነው የቀጠሉ የአንዳንድ ድርጅት አመራሮችና የሚድያ ባለቤቶች በአፋህድ አመራሮች ላይ የከፈቱት የስብእና አገዳደል እጅግ በጣም አሳፋሪና ወደፊት የአማራ የህልውና ታሪክ ሲጻፍ የማይረሳ ነው። ይህ ከአማራነት ስነምግባር ያፈነገጠ የስም ማጥፋት ስልት ንቅናቄው ከተመሠረተም በኋላ በአዲስ አመራሮችም ተሳትፎ ጭምር እንደቀጠለ ነው። ለዚህም የንቅናቄው ወታደራዊ አዛዥ እና የሕዝብ ግንኙነቱ መምሪያ ሃላፊ የትግሉ የጀርባ አጥንት የሆነዉን ዲያስፖራን ለማሸማቀቅ ሰሞኑን ያስተላለፏቸዉ አፍራሽ መልዕክቶች በቂ ማስረጃዎች ናቸው። በበኩላችን የስም ማጥፋት ዘመቻ የተቀደሰውን የአማራ የህልውና ትግል ፈጽሞ አይመጥንም ብለን እናምናለን።
6ኛ. ሰሞኑን የአፋብን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሚድያንና የሚድያ ባለቤቶችን አስመልክቶ ንቅናቄው “የሚሰጠውን አቅጣጫ ባለመከተል የሚጽፉና የሚዘግቡ ወይም የሚተቹ ጠላትነታቸው በሕዝቡ እንዲታወቅ እናደርጋለን” ይላል። ይህ የጥርነፋ ሥራ በጣም አስደንጋጭ ነው። እኛ ብቻ
ነን የምናውቅልህ፣ አፍህን ለጉመህ ተከተለን እንደማለት ነው። በተጨማሪም የአፋብን የወታደራዊ ሥልጠና መምሪያ ሃላፊ ከኛ ጋር የማይሰለፉ ፋኖዎችን ትጥቅ እናስፈታለን፣ እርምጃም እንወስዳለን ሲል ተሰምቷል። እነዚህና ከላይ የጠቀስናቸው ሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶች የሚያረጋግጡት ንቅናቄው የተመሠረተው በመተማመን ላይ ሳይሆን በእጅ ጥምዘዛ ላይ እንደሆነ ነው። በተለይ በ02/04/2026 ንቅናቄው ባደረገው ሕዝባዊ ውይይት ላይ ጎልቶ የተንፀባረቀው አንድነት ሳይሆን አምባገነንነት ነው። ስለሆነም ይህ ዓይነቱ የንቅናቄው አዝማሚያ ያስደነገጣቸው ፋኖዎች ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉለትን የህልውና ትግል እየተው በየጊዜው ወደየመጡበት እየተመለሱ ለመሆኑ የማይካድ መራር ሃቅ ነው።
በዚህ አጋጣሚ መግለጽ የምንፈልገው ንቅናቄው ይፋ ከመሆኑ ቀናትና ስምንታት በፊት ከሕወሃት ጋር አጋር የመሆን ጉዳይ አሳስቦናል በማለት የህልውና ትግሉን ትተዉ፣ በሥራቸው የነበሩትን ፋኖዎች ሜዳ ላይ በትነው ለብልፅግና እጃቸውን የሰጡትን “የፋኖ አመራሮች” እጅግ በጣም የምንጠየፋቸውና የምናወግዛቸው መሆኑን ነው። ከዚህ በላይ የክህደት ጥግ ሊኖር ይችላል ብለንም አናምንም።
እንደድርጅታችን አንድነት አመለካከት የአፋሕድና አፋብሃ አንድነት ብዙ መደፈን ያለባቸው ክፍተቶች እንደአሉት ተገንዝበናል። የፋኖን አንድነት እንደመርህ ምንጊዜም የምንቀበል ብንሆንም ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች አፋብንን የምናየው ምሰሶዉ በወጉ መቆም ያልቻለ፣ ጣራው ያልተከደነ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሥራዎች የሚቀሩት ጎጆን አድርገን ነው። በሌላ አነጋገር የአንድነት ሥራው ተጀምሯል። ግን አልቋል ብለን እራሳችንን ካሞኘን የምንጎዳው ትግሉን ነው። የሚጠቀሙት ደግሞ የአማራ ጠላቶች ናቸው። የጎደለውን ማሟላት የሁሉም ባለድርሻ አካሎች ሃላፊነት ስለሆነ ሸፍጥን፣ ጎጠኝነትን፣ ማናለብኝነትን፣ ግለኝነትንና አግላይነትን ባስወገደ፣ እንዲሁም ጠላትና ወገንን በለየ መልኩ ቆም ተብሎ ታስቦና
ተስተንትኖ የተጀመረው የአንድነት ቤት በማይነቃነቅ መሠረት ላይ እንዲገነባ አጥብቀን እናሳስባለን።
ዘላቂ አንድነት ለጋራ አሸናፊነት!
አንድነት ለአማራ ኅልውና (አንድነት)
ጥር 30, 2018





Comments