በህዝብ የተገነባ ሚዲያን ተጠቅሞ የግል ፍላጎትን ማሳካት አይቻልም!!! ከአንድነት ለአማራ ህልውና ትግል (አንድነት) የተሰጠ የአቋም መግለጫ
- Amhara Unity
- Oct 18, 2025
- 1 min read

በህዝብ የተገነባ ሚዲያን ተጠቅሞ የግል ፍላጎትን ማሳካት አይቻልም!!!
ከአንድነት ለአማራ ህልውና ትግል (አንድነት) የተሰጠ የአቋም መግለጫ
በዘመናት በተፈበረከ የሃሰት ትርክትና ዘመን ወለድ ጥላቻ እየተገደለ:እየተሳደደ እና ሃብት ንብረቱ እየወደመ መከራና ስቆቃ የበዛበት የአማራ ህዝብ ደምና አጥንቱን ገብሮ ባቆማት ሃገሩ ላይ በህይወት መኖር ተከልክሎ እንደ ሰው ቀርቶ እንደ እንስሳት እንኳን መኖር ተነፍጎ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ችሎ ለመቆየት ቢሞክርም ጊዜ ወደ ወንበር ያመጣቸው ጠላቶቹ ይባስ ብለው ደጁ ድረስ ሄደው ሊያጠፋት ጠብመንጃ ሲያነሱ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ራሱን ወደ መከላከል የህልውና ጦርነት ከገባ ሁለት አመታትን ተሻገረ።
ይህን የወገናችንን መከራ ቆመን አናይም ያሉና ከአማራ አብራክ የወጡ በተለያየ የአለም ክፍል የሚገኙ የዲያስፓራ አባላትም ለትግሉ ይመጥናል የሚሉትንና ለውጥ እናመጣለን ብለው በመረጡት አደረጃጀት በመሰባሰብ የየድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ መሬት ላይ ያሉት አርበኞችም ሆኑ መላው የአማራ ህዝብ የሚያውቀው እውነት ነው ።
በዚህ የህልውና ትግል እንቅስቃሴ ላይ ያሉትን ጉድለቶች ሳይንሳዊ በሆነ የፓለቲካ ትንተናና ትግሉ ከሚጠብቀው ሁለገብ ድጋፍ አንፃር የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት እና የተበታተነውን የአማራ ፋኖ ትግል ወደ አንድ ወጥነት ያለው አደረጃጀት እንዲመጣ ለማገዝ ከተቋቋመበት ቀን ጀምሮ የተረዱት በጣም ብዙዎች ቢሆኑም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እንደ አፍራሽ አደረጃጀት በመፈረጅ “አንድነት” መጣላችሁ የሚል የተዛባ ሃሳብ የሚያስተጋቡ ጥቂት ግለሰቦች እንዳሉ ከማህበራዊ ሚዲያና በጥቅምት 6/2018 ዓ.ም በኢትዮ 360 የቀጥታ ስርጭት ላይ በሁለት ጋዜጠኞች የቀረበውን በማስረጃ ያልተደገፈ ፍረጃ ሰምተን ለሁሉም የትግል ደጋፊዎች እውነተኛውን የ”አንድነትን” አቋም በድጋሚ ለማብራራት ተገደናል ።
በእለቱ በቀረበው ውይይት ላይ ድርጅታችን “አንድነት” ገና ከምስረታው ቀን ጀምሮ ሊያሳካቸው ያቀዳቸውን ጉዳዮች በዚሁ መገናኛ ብዙሃን ቀርበን በዝርዝር ያስረዳን ከመሆናችንም ባሻገር በበራሪ ወረቀቶች (flyers ) ጭምር በማሰራጨት አላማው፣ ረዕዩ፣ ተልእኮውንና ስትራቴጂካዊ ምልከታዎቹን በግልጽ አሰቀምጠን ሳለ ከየትኛዎቹ ድርጅቶች ጋር ተቆጥሮ እንደሆነ ባይገባንም “ሦስተኛ አደረጃጀት “በሚል የተደረገው ገለፃ ፍፁም ከእውነት የራቀ ከመሆኑም በላይ መረጃን በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብን ጠንቅቀው የሚያውቁት ሁለቱ ጋዜጠኞች “አንድነት የሚባለው ሰራዊት እያደረጀ ነው” የሚል በቦታ፣ በጊዜና የተደራጁትን አካላት ጭምር በስም መግለፅ የሙያ ግዴታ መሆኑ እየታወቀ “እነማን” እንደሆኑ በመረጃው አልተገለፀም የሚል እርስ በእርሱ የሚጋጭ መልእክት ማስተላለፍ “አንድነት”ን እንደ ሰጋት ከማየት ወይንም ከግለሰብ ፍላጎት የተነሳ ለሚዲያው የማይመጥን የስም ማጥፋት እና አላማችንን በውል ተረድቶ ከጎናችን የተሰለፈውን ሥር ነቀል ለውጥ ናፋቂ የአማራ ዲያስፓራ ግራ ከማጋባት የዘለለ ውሃ የማይቋጥር ውንጀላ መሆኑን ደግመን ለመግለጽ እንወዳለን ።
ከተደረገው ውይይት በእጅጉ የሚያሳዝነው እና በራስ ስሜት ወይንም በሌላ ገፊ ሃይል በተፈጠረ ምናብ ከ”አንድነት” ጋር በቀጥታ ስማቸው የተጠቀሰው የሸዋና የጎንደር ጠቅላይ ግዛቶችን የሚመለከት ፍረጃ ለማስተላለፍ የተፈለገው አጀንዳ ምን ሊሆን ይችላል ብለን እኛም እንድናጤነው የትግሉ ደጋፊዎችም የዚህ መሰል የተወሰኑ አካባቢዎችንና መሪዎችን ጭምር ለመጠቃቀስ የተሞከረበት ዝግጅት ከበስተጀርባ ያዘለው ተልዕኮ ምንድነው ብለው በጥንቃቄ እንዲመረምሩት ለማስታወስ እንገደዳለን ።
የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል የመቋጫው ምዕራፍ ላይ እየደረሰ ባለበትና መሬት ላይ ያሉት የፋኖ አደረጃጀቶች የውስጥ ልዬነቶችን እያጠበቡ ወደ አንድነት በመጡበት ወቅትና በጎጃም የትንሿ እህታችን በአለምላይ ዋሴ የጠላት የጭካኔ ሰይፍ አርፎባት መስዋዕትነት መክፈሏን በተደራጀ መንገድ መዘከር ለዚህም ሚዲያው ቀዳሚ ሆኖ መገኘት በሚጠበቅበት እለት “እንዲህ ተባለ” የሚል ያልተጨበጠ መረጃ ብዙ ህዝብ በሚከታተለው የቀጥታ ሥርጭት ማስተላለፍ “እውነት ለትግሉ መጨነቅ ነውን?” ብለን ደጋግመን እንድንጠይቅ እድል ከመክፈቱ ውጪ እንደ ጋዜጠኛ የሁለቱንም ወገን መረጃና ማስረጃ መርምሮ እውነቱን ማቅረብ እየተቻለ በደፈናው “አንድነት” መሬት ላይ ፋኖ እያደራጀ ነው የሚለው ውንጀላ በጠላት በኩል ለተሰለፉ ግለሰቦች የሚዲያ ግርግር ይጠቅም ካልሆነ በሰተቀር ድርጅታችን “አንድነት” የአማራ ፋኖን የህልውና ትግል በሁለገብ ድጋፍ ከማገዝና በወንድማማቾች መካከል የሚፈጠሩ ልዬነቶች እየጠበቡ አማራዊ አንድነት እንዲፈጠር ከመደገፍ የዘለለ የራሱ ታጣቂ የሚያደራጅበት የህግም የአሳብም ሆነ የሞራል ዝግጅት የሌለው መሆኑን በድጋሚ ሁሉም አማራ ይወቅልን እንላለን ።
በመጨረሻም በውይይቱ ላይ የመሪዎቻችንን ስም ጭምር በመጥራት የተደረገው የሃሰት ትንተና ድርጅታችን “አንድነትም” ሆነ በስስት የምንደግፋቸው የፋኖ (የአፋህድ) መሪዎች በሌሉበት በሃሰት የቀረበ ውይይት በመሆኑ የዚህ መሰል በህዝብ ድጋፍ በተገነባው የሚዲያ ተቋም የራስን ፍላጎት ለማስፈፀም የሚደረገው እንቅስቃሴ ከወዲሁ እንዲታረም በጥብቅ እያሳሰብን “አንድነት ለአማራ ህልውና ትግል” (አንድነት) እንደ ስሙ የነጠረ አቋም ያለውና በእውቀትና እውነት የሚመራ የሁሉም ሥር ነቀል ለውጥ ደጋፊ አማራውያን ቤት በመሆኑ በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ሁሉ በጋራ አብሮን እንዲቆም ወገናዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ።
ዘላቂ አንድነት ለጋራ አሸናፊነት!
አንድነት ለአማራ ህልውና ትግል (አንድነት)
ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም
ሰሜን አሜሪካ



Comments