ሰላማዊ ሰዎችን በመጨፍጨፍ የአማራን ህልውና ትግል ማስቆም አይቻልም!
- Amhara Andnet
- Oct 7, 2025
- 3 min read
Updated: Oct 8, 2025
(ከአንድነት ለአማራ ኅልውና ትግል የተሰጠ መግለጫ)

“በሦስት ሳምንት ቀበቶውን አስፈታለሁ” ብሎ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘመተው የአገዛዙ ሠራዊት ሦስተኛ ዓመቱን ባስቆጠረ ሽንፈት ላይ ይገኛል፡፡ በሁሉም ግምባር በሚባል ደረጃ በፋኖ እየተሸነፈ መሆኑን ተከትሎ በየጊዜው የጦር ወንጀሎችን ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ ከሰሞኑ በሰሜን ወሎ በጦር አውድማ ያልተሳተፉ ንፁሀንን በጅምላ በድሮን በመጨፍጨፍ ላይ ይገኛል።
ይህም የአገዛዙ አረመኔነት የአማራን ሕዝብ ይበልጥ ቢያስቆጣው እንጂ የተለየ ውጤት አይኖረውም።
የጦር ወንጀለኛው የብልጽግናው አገዛዝ ከቀደምት ባህሪዎቹ ስንነሳ ከፋኖ ከፍተኛ ምት ሲደርስበት ንጹሃንን ማጥቃት፤ የማኀበራዊ ተቋማትን ማውደም፤ የአርሶ አደሮችን ማሳ ማቃጠል፤ የእምነት ቦታዎች ላይ ጥቃት መፈጸም የተለመደ የጦር ወንጀል ድርጊቶቹ ናቸው፡፡
የዕለት ኑሯቸውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በሚሉ፣ ከውጊያው አውድ ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ሰላማዊ ወገኖቻችንን በጅምላ ገድሏል፣ ንብረታቸውን አውድሟል፡፡ መሰረተ ልማቶችንም አፈራርሷል፡፡
የዚሁ የጦር ወንጀሉ አካል የሆነው መስከረም 17/2018 ዓ.ም. በሰሜን ወሎ ዞን፣ ጉባላፍቶ ወረዳ በሳንቃ ጤና ጣቢያ፣ የድሮን ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመበት ቦታ ምንም ዓይነት የውጊያ አውድ ያልነበረበት ከመሆኑም በላይ የህክምና ማዕከል መሆኑ የአገዛዙን የጦር ወንጀል የከፋ ያደርገዋል፡፡
የድሮን ጥቃቱን ተከትሎ ማዋለጃ ክፍል ውስጥ እንዳለች የተገደለችውን እናት ጨምሮ 4 ንጹሃን ተገድለዋል። አንድ የ6 ዓመት ልጅ እና ወላጆቿ እንዲሁም 8 የጤና ጣቢያው ሠራተኞች ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። የጤና ጣቢያው ትልቅ ጉዳት ደርሶበታል።
በአጠቃላይ በሰሜን ወሎ ባለፉት 10 ቀናት የሕክምና ጣቢያዎችንና ትምርት ቤቶችን ጨምሮ ንጹሃንን እና መሰረተ ልማቶችን ማዕከል ያደረጉ ከ14 ያላነሱ የድሮን ጥቃቶች በአገዛዙ ተሰንዝረዋል።
በተጨማሪ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሥርዓቱ ባሰማራቸው በኮሬ ነጌኛና ጋቼና ሲርና ገዳይ ቡድኖች እንዲሁም በክልሉ ልዩ ሃይልና ሚልሺያ በአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም ላይ ይገኛል።
በኦሮሚያ ክልል በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት አባቶች እና ምእመናን ላይ በተለይ በምሥራቅ አርሲ በየጊዜው የሚደርሰው ጥቃት እንደቀጠለ ነው።
በአማራ ህዝብ የታወጀው ማንነት ተኮር የጅምላ ጭፍጨፋ ለአራት አሥርተ ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ስልታዊ በሆነ መንገድ በድብቅ ነበር። ባለፉት ሰባት ዓመታት በአብይ አህመድ አገዛዝ በአማራ ላይ የሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ ግልጽና ተጨባጭ ሆኗል፡፡
ከሁሉም በላይ አሳሳቢ ነገር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሥርአቱ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጽማቸውን ማንነት ተኮር ወንጀሎች ትኩረት ትኩረት እንደነፈጋቸው መሆኑ ነው። ኃላፊነቱን ለመወጣት ፈቃደኝነት እያሳየ አይደለም፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወንጀለኛውን አብይ አህመድን ተጠያቂ በማድረግ ፋንታ፣ ከአይ ኤም ኤፍ (IMF) እና የዓለም ባንክ (World Bank) በቢልየን ዶላሮች የሚቆጠር ብድር እንዲያገኝ አድርጎታል። ይህም የጦር ወንጀለኛውን አብይ አህመድና አገዛዙን የልብ ልብ እንዲሰማው አድርጎታል፡፡ ከመቼውም የበለጠ ወራሪ ሃይሉን በአማራ ክልል አሰማርቶ በሰማይ በድሮን፣ በምድር በዘመናዊ ተወንጫፊ መሣሪያዎች የአማራን ሕዝብ እየጨፈጨፈው ይገኛል።
ዛሬም እንደትናንትናው የአማራ ሕዝብ ስቃይና መከራ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትኩረት ተነፍጎታል፡፡ በየጊዜው የሚወጡ ሪፖርቶች በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ በጥልቅት አይመለከቱም፤ ለዚህ የቅርቡን የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በኢትዮጵያ የውጭ ኢንቬስትመንትን ሪፖርት ማየት ይቻላል፡፡
የአማራ ሕዝብ የጅምላ ሞት የማያስደነግጠው ዓለማቀፉ ማኀበረሰብ፣ የሞራል ተጠያቂነት አለበት፡፡
የኛ ጥያቄ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስከመቼ ነው የአብይ አህመድ አገዛዝ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ዝም ብሎ የሚያየው የሚል ነው።
በተለይም 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በመላው ዓለም ያሉ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ጥረት እያደረገ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፣ የትራምፕን አስተዳደር ጨምሮ ዓለማቀፉ ማኀበረሰብ በአማራ ሕዝብ ላይ የተከፈተውን የዘር ማጥፋት ዓላማ ያለው ጦርነት በቸልታ መመልከቱ አሳዝኖናል፡፡
የዓለማቀፉ ማኀበረሰብ ዝምታ ለዘመናት ያዳበሩትን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪነት እና በመላው ዓለም ያሉ ግጨቶችን እና ጦርነቶችን በሰላም ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ሰፊ ጥረት የሚያግዝ ሆኖ አላገኘነውም። እንዲያውም፣ በተቃራኒው፣ አገዛዙ በጦርነት ፖሊሲው እንዲፀና፣ እራሳቸውን ከመንግሥታዊ የጅምላ ጭፍጨፋ መከላከል የማይችሉ ንጹሃን ደግሞ በታወጀባቸው የዘር ማጥፋት ዓላማ ያለው ጦርነት ይበልጡኑ እንዲጠቁ እንዳያደርጋቸው ስጋት አለን።
ስለሆነም፡- ዓለማቀፉ ማኀበረሰብ የብልጽግና አገዛዝ በራሱ ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ ሌሎች የጦር ወንጀሎችን የሚመረምር ገለልተኛ የሆነ ዓለምአቀፋዊ አጣሪ ቡድን እንዲቋቋም እና በውጤቱ መሠረት ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፡፡
ድል ለአማራ ፋኖ!
ድል ለአማራ ሕዝብ!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
አንድነት ለአማራ ኅልውና ትግል (አንድነት)
መስከረም 24/2018




Comments